|
ዶ/ር አክሎግ ቢራራ
በቁጥር ሰባት የደመደምኩት፤ አገርን ከአስከፊ አደጋ ለመከላከል ከተፈለገ፤ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰው ርህራሄ ከሌለው፤ ዘርፎ ለዘራፊ ዳራጊ ከሆነ የዘረኛ ስርአት አላቆ ለፍትሃዊ አማራጭ የሚቨጁ አገር አቀፍ ተቋሞችን መገንባት ያስፈልጋል። አለበለዚያ፤ አገራችን ሁልጊዜ ያልተረጋጋ ች ሆና ትቆያለች፤ ህዝቧም በድህነት አለንጋ ሲገረፍ፤ ወጣቱ ሲስደድ ይኖራል። መፍትሄው በእጃችን ነው። ይህን አስፈላጊ ለውጥ ለማድረግ የባህል፤ በመጀመሪያ፤ ያስተሳሰብ፤ የአሰራር፤ የአደረጃጀትና የአመራር ለውጥ መጀመር አለበት (Paradigm shift in thinking, organization and
leadership)። ለፍትሃዊ ለውጥ የሚደረግ ጉዞ የማንኛውም አገራዊ የሆነ ተቃዋሚ ግለሰብ፤ የማንኛውም ማህበራዊና የፖለቲካ ድርጂት፤ የማንኛውም ብሄር፤ የማንኛውም ሃይማኖት ተከታይ፤ ወዘተ አላማ መሆን ይኖርበታል። የውጭ ጠላቶች፤ የውስጥ ደጋፊወች ባጠመዱልን “የከፋፍለህ ግዛው ክልል” ወጥመድ ከቆየን አሰቃቂውን የህወሓት/ኢሃዴግ አገዛዝ ለመለወጥ አንችልም። እነ “አቦይ ስብሃት” የሚናገሩት ፕሮፓጋንዳ ይቀጥላል።
የጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን ከሞት አፋፍ ያደረሰ ህመም (Critical illness and condition) በቅርብ የሚያውቁ ታዛቢወች እንደሚሉት ከሆነ፤ በህይወት መቆየታቸው ያጠራጥራል። ቢቆዩም፤ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያን ሊገዙ/ሊመሩ አይችሉም። ስለሆነም፤ ተተኪ መሪ ወይንም መሪዎች መሰየማቸው አይቀርም። የገነቡት አገዛዝ ይቀጥላል። ለዚህ ሽግግር ከጀርባ ሆኖ ድጋፍ የሚሰጠው የአሜሪካ መንግስት ነው። ህወሓት/ኢሃዴግ፤ የአሜሪካ መንግስት፤ ኢንቬስተሮችና ሌሎች ደጋፊወች የመለስ አገዛዝ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ። መረጋጋት (Stability)ተደጋጋፊ ጥቅም ስላለው።
በሌላው አንጻር ሲታይ ግን፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብና በአፍሪካ ቀንድ ያንዣበበውን የአልካይዳ ሆነ ሌላ አደጋ በዘላቂነት ለመከላከል፤ ብዙ ቢሊየን ዶላር ለሚያፈሰው የአሜሪካ መንግስት፤ ዘላቂና አስተማማኝ ጥቅም ሊያስገኝ የሚችለው አገዛዝ የህወሓት/ኢሃዴግ መንግስት አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ያውቃል፤ የአሜሪክ መንግስት የኢትዮጵያ ሕዝብን ፍላጎት ቸል ብሎታል። ዘላቂነትና ፍትሃዊ የሆነ አገዛዝና እድገት እውን የሚሆነው፤ በህዝብ የተደገፈ፤ በህግ የበላይነት የተመሰረተ፤ ፍትሃዊነቱ የተረጋገጠ፤ ተቋሞቹ አገራዊ የሆኑ፤ መንግስቱ፤ አስተዳደሩ፤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አገልጋይ የሆነ፤ ባጭሩ፤ ለህዝብ ተወካይ የሆነ አገዛዝ (Governance) ሲገነባ ብቻ ነው። ይህን ለማድረግ፤ ህወሓት/ኢሃዴግ መፍርስ አለበት። ይህን አማራጭ የማቀርብና የመደራደር ተግባርና ሃላፊነት የተቃዋሚው ክፍል እንጂ፤ የህወሓት ወይንም የአሜሪካ መንግስት አይደለም። ስለሆነም፤ ለአንድ አገራዊና ህዝባዊ ስር ነቀል እንቅስቃሴ ካሰብን፤ በመቻቻል ተነስተን በስራ የምናሳይበት ወቅት አሁን ነው። መግለጫ ማውጣት በቂ አይደለም። በመጀመሪያ እድሎች በፍጥነት እያመለጡን መሆኑን መቀበል አለብን።
በ July 17, 2012, Thomas Mountain የተባለ አስመራ የሚኖር ጋዜጠኛ ስለ መለስ ዜናዊ መንግስት “መፈራረስ” (Crumble) ና ሰለ ኢትዮጵያ መጥፋት የደረሰበት ድምዳሜ ሊሆን/ላይሆን ይችላል። እኔ ኢትዮጵያ ትጠፋለች ብየ አልቀበልም። እሱ መሆኑ አይቀርም ባይ ነው። አስመራ ተቀምጦ ይህን ቢል አያስገርምም። የኢትዮጵያ በዘር ተከፋፍሎ የመጥፋት ሴራ የተጠነሰሰው በውጭ ጠላቶቿና በኤርትርያ ተገንጣይ ቡድኖች ነው። አሁንም መጥፋቷን ስራ ላይ ለማዋል የተዘጋጁ እንዳሉ አንጠራጠር። እ.አ.አ.በ 1993 መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ “ከመቶ አመታት አይበልጥም፤ ከዚህ የተለየ ነው ብለው የሚቃዡ ግለሰቦች የሚያወሩት ልብ ወለድ ነው” ያሉት ከሚያደንቁት ኢሳያስ አፈወርቂና ከሌሎች ጸረ ኢትዮጵያ ከሆኑ ግለሰቦችና ግንባሮች የተማሩትን ነው። ህወሓት የተጸነሰው በዚህ መሰረታዊ ፍልስፍና ነው። ስለሆነም፤ አደጋው አሁንም እያንዣበበ ነው። አገርን ለመታደግ የምንፈልግ ግለሰቦችና ድርጂቶች ይህን የሚያንዣብብ አደጋ በጥልቅ ካላየን፤ ለዚህ አማራጭ ለመስጠት ብቁ ሁነን ካልደረስን፤ ታሪክ የሚወቅሰው ኢሳይያስን ወይንም መለስን ሳይሆን እኛን ነው። እነሱ አላማቸውን ያውቃሉ፤ እኛ አላማ ቢስ ሁነን እንታያለን። ይህ ሁኔታ በፍጥነት መለወጥ አለበት።
ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ እንቁም/እንናግር፤
አሜሪካኖች በአሁኑ ወቅት የመለስን መታመም በማጤን፤ አድራጊ ፈጣሪ (Power brokers) ሁነው አማራጮችን ለእኛ በምስጢር ሲደራደሩልን፤ አገር አቀፍ የሆነው የተቃዋሚ ድምጽ የት ሄደ ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው። እኛስ አገራችን ለማስቀደም ምን እየሰራን ነው? ተባብረን ድምጽ እያሰማን ነው? ለምድን ነው አነድ አገር አቀፍ የሆነ፤ ሁሉንም የሚያካትት/የሚያነጋግር፤ በኢትዮጵያ አንድነት፤ በመላው ሕዝቧ እኩልነትና ሉአላዊነት፤ በሰብአዊ መብቶችና ክብር፤ በነጻነት፤ በፍትህ-ርትህ፤ በህግ የበላይነት፤ በነጻ ምርጫ፤ ወዘተ መስፈርቶች የሚመራ አለም አቀፍ ስብሰባ (a Grand National Coalition) አሁን ለማድረግ የማንነሳው ብለን መጠየቅ አለብን። አገራችን ከአደጋ ለማዳን ከፈለግን፤ የምንቃወመውን የጭቆና አገዛዝ ለመለወጥ ፍላጎት ካለን፤ ይህ ታላቅ ጥምረት (Grand Coalition)፤ ሽግግር ምን እንደሚመስል አገር ቤት ካሉ አገር አቀፍ ከሆኑ ተቃዋሚ ድርጂቶች ጋር በመወያየት አግቫቭ ያላቸውን አማራጮች መቅረጽ ይኖርባቸዋል። ሽግግሩ ወደ ዘላቂ መፍትሄ ሊመራ የሚችለው፤ ኢትዮጵያን ከአደጋ ለማዳን፤ አብሮ በመቻቻል ለመኖር፤ ፍትሃዊ ስርአት ለመገንባት የሚፈልጉ ሁሉ ሲካተቱና ሲሳተፉ ነው። ህወሓት/ኢሃዴግ ተካፋይ እንዲሆን ያልተቆጠበ ጥረት መደረግ የሚኖርብት ይህን አላማ በማጤን ነው።
በእኔ ግምት፤ ህወሓትና እሃዴግ ውስጥ እርቅን፤ መቻቻልን የሚፈልጉ አሉ፤ እነዚህን መሳብ፤ ማነጋገር፤ መቅረብ ጥበብ ነው። የበላይ አዛዡ ህወሓት(ትግሬ) ቢሆንም፤ የአገራችን የጦር ሃይል ከሁሉም ህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጣ ነው። ተራው ሰራዊት ለሃገር እንዲያስብ ማድረግ የሁላችንም ሃላፊነት ነው። የውጭ መንግስታት፤ በተለይ፤ የአሜሪካ መንግስት ይህን የእርቅ፤ የመመካከር፤ አማራጭ ለመቀበል የሚገደድበት ምክንያት እንዳለ በተደጋጋሚ አሳይቻለሁ።
ይህን አላማ እውን ለማድረግ መጠየቅ ያለብን ጉዳይ “ኢትዮጵያዊያን፤ ነገሮች ከመበላሸታቸው፤ ሁኔታወች ከቁጥጥር ውጭ ከመድረሳቸው በፊት አማራጮችን በጋራ ተወያይተው፤ በጋራ ለማቅርብ የሚችሉት” ቀን መቸ ነው፤ የሚጎተቱስ በምን ምክንያት ነው የሚለውን ጥያቄ በማቅረብ ነው። የተማረው፤ አገር ወዳዱ፤ በመድብለ ፓርቲ፤ ወዘተ የሚያምን ሁሉ መሰብሰብ፤ መነጋገር፤ መመካከር፤ አማራጮችን ማቅርብ ያለበት ያለመሰብሰብ/ያለመተባበር አደጋን በማየት ነው፡፡ የምእራብ አገሮች፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ወዘተ ሊያከብሩን የሚችሉት ብቃት ያለን መሆኑን፤ ሃላፊነት የሚሰማን መሆኑን በተግባር ስናስመሰክር ብቻ ነው። ወሬ ስለተወራ ብቃት አይደለም፤ ስራ ስለተሰራ ብቻ ነው። የሃገራችን ሕዝብ ዋና ጥሪ መመለስ ብቃት ያሳያል። ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ አለሁ የማለት ጥያቄ ፋታ እነደማይሰጥ መገንዝብ የብቃት መለኪያ ነው።
አሁንም ክፍፍል እየጎዳን ነው፤
መጠንቀቅ ያለብን ግን እኛ ተበታትነን፤ ኢትዮጵያን ካለባት አደጋ ልናድን አንችልም። አማራጭ ለመስጥት አንችልም። ኢትዮጵያ ከፈራረሰች ዋጋ ከፋዩ አንድ ብሄር፤ አንድ ሃይማኖት፤ አንድ መደብ ወዘተ አይሆንም። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከባድ ዋጋ ይከፍላል። የመገንጠል፤ የእርስ በእርስ ጦርነትን ጉዳት ባለፉት አስርት አመታት አይተናል። የባህር በር ማጣት ያመጣውን ጉዳት ብቻ ማየት ይበቃል። ችግሩን ሳጤነው የምፈራው አበይት ነገር፤ የማናየው/ የምናየው ተደጋጋሚ ድክመት አለ። አሁንም ወርቃማ የሆኑ፤ አገርን ከክፋ አደጋ ለማዳን፤ የነጻነትና የመልካም አስተዳደር ድልድይ ለመዘርጋት የሚያስችሉ፤ ተጨባጭ ሁኔታወች የፈጠሩት እድሎች እያመለጡን ነው። እስካሁን ልንጠቀምባቸው አልቻልነም። የተማረው የሰው ሃይላችን አያል ቢሆንም፤ የሃገራችንና የወገኖቻችን እድል የሚወስኑት ምእራባዊያንና የእነርሱ ደጋፊ የሆኑ ጥቂት ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ለምን? በመከፋፈላችን። ስለሆነም፤ የእኛ መኖር፤ የእኛ መማር፤ የእኛ ድርጂት ማቋቋም ለኢትይጵያና ስብጥር (Diverse) ሕዝቧ ትርጉሙ ምንድን ነው ብለን መጠየቅና መልስ መስጠት ተገቢ ነው።
አገራዊ የሆነ፤ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊነት በሩ ክፍት የሆነ አገር አቀፍና ከብሄር በላይ የተደራጀ የፖለቲካ ተቋም በህወሓት መዳከሙ፤ በብልሃት፤ በጥበብ፤ በአርቆ አሳቢነት፤ በመቻቻል፤ መለኪያውች የሚዳኝ አመራር አለመኖሩ አደጋውን አባብሶታል። የነጻነት ጉዞውን ገትቶታል። ለዚህ ነው፤ አሜሪካኖች ለእኛ እየወሰኑ ያሉት። መኖራችን ያልተቀበሉት ስለተከፋፈልን ብቻ ነው። ማውንቴን የተባልው ጋዜጠኛ ይህን ድክመት ስላየ፤ ኢትዮጵያ ትበታተናለች ብሎ በእኛ አገር እጣ ላይ ደመደመ። ቴሬንስ ላየንስም በቅርቡ ያወጣው ዘገባ ይህን ያለመረጋጋት አደጋ ያመለክታል። አንዳንዶቻችን፤ ጋዜጠኛው አስመራ ሆኖ ህወሓትን ስለሚቃወም ጉዳቱን አልተረዳነም። የተቃዋሚው ክፍል መበታተኑ፤ በብሄር የተደራጁና የታጠቁ ክፍሎች “አላማችን መገንጠል ነው” ማለታቸው ለህወሓት አመራርና ለአሜሪካ መንግስት ሚና ፋታ ሰጥቷል። የአሜሪካ መንግስት (የውጭ ጉዳይና የስለላ ድርጂቶች ልኡካን በመጠቀም) ከመቸውም ጊዜ የበለጠ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ውሳኔወችን የሚሰጥበት ምክንያት የመፈራረስ አደጋውን ስላየ፤ የአካባቢውን አደጋ ስለመዘነ፤ተቃዋሚው ክፍል መከፋፈሉንና በአንድ አገራዊ አጀንዳ አለመቆሙን ስለተገነዘበ ነው።
አሜሪካ የወሰደው እርምጃ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደህንነት፤ ለሃገራችን አንድነትና ጥንካሬ አስቦ ሳይሆን፤ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን አደጋ ለመከላከል፤ የአሜሪካን ጥቅም ለማስከበር፤ ለዚህ ታማኛ የሆኑ መሪወችን ለመመልመል ነው። እኛ በአንድ ላይ ሁነን ድምጽ ብናሰማ፤ ቢያንስ ሽግግሩን ለማሻሻል እንችላለን የሚል ግምት አለኝ።
ይህን አደገኛ ሁኔታ እያየን፤ አሁንም የምንዳኘው፤ ጊዜ ባለፈበት የግለሰብ፤ የራስ ቡድን አደረጃጀትና አመራር ነው። ትኩረታችን ተቃዋሚው ክፍል ምን አማራጭ አዘጋጅቷል በሚለው ተፈላጊ ቁም ነገር ላይ ሳይሆን፤ በህወሓት መሪ ላይ የደረሰውን ህመም በሚመለከት ሁኗል። ብንወድም፤ ባንወድም፤ ብንቀበልም ባንቀበልም፤ ማውንቴን አስመራ ሆኖ ቢበይን/ባይበይንም፤ የህወሓት አመራር ራሱን ስለመተካካት (Succession) እቅድ ካወጣ ቆይቷል። በተቃዋሚው ክፍል ያለውን ሁኔታ ስናይ ግን እንኳን ከዚህ ደረጃ ለመድረስ (ተተኪ ለማዘጋጀት ቀርቶ)፤ አሁንም እርስ በእርሱ ለመተማመን፤ ለመፈላለግ፤ በዙር ጠረጴዛ ተቀምጦ ስለ ሃገር፤ ሰለወገን ለመነጋገር አልቻለም። ህወሓት ያዘጋጀው የመተካካት አማራጭ የሚገዛው ለአንድ አላማ ብቻ ነው። ተተኪወች የሚመረጡት በታማኝነት፤ በስርአቱ ጠባቂነት፤ በአሜሪካ ጥቅም አገልጋይነት፤ በጥቅም፤ ተብሎ እንጂ የነጻነት ለውጥ ሃዋርያት በመሆናቸው አይደለም። ሊሆንም አይችልም። አንዳንድ ተመልካቾች የሚሉት፤ ተተኪወቹ የባሰ “ተኩላ፤ የባሰ በዝባዥ፤ የባሰ ጨቋኝ” ወዘተ ይሆናሉ የሚል ነው። ሌሎች ደግሞ፤ የተሻለ ሁኔታ ይፈጠራል ይላሉ። ሊሆኑ፤ ላይሆኑ ይችላሉ። ዋናው መነጋገሪያ መሆን ያለበት የመለስ ተተኪ የህወሓት አባላት ምን ያደርጉ ይሆን የሚለው፤ በምንም ልንቆጣጠረው የማንችለው ጉዳይ አይደለም። እኛ ማድረግ ያለብን ከመለስ ባሻገር አይተን የተቃዋሚው እምቅ ሃይል (Potential Force) አሁን ምን መስራት ይገባዋል የሚለውን አንገብጋቢ አገራዊ/ወገናዊ ጥሪ ነው።
የተዳፈነ እሳት ሲቀጣጠል፤
በአሁኑ ወቅት፤ ለግለሰብና ለህብረተሰብ ደህንነት፤ ለሰባዊ መብቶች፤ ለሃይማኖት መብት፤ ለነጻነት፤ ለፍትህ-ርትእ፤ ለህግ የበላይነት በተከታታይ የሚታገለው ተራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። በዚህ ዲሞክራሳዊ የሆነ የህዝብ ትግል ድምጻቸውና አቋማቸው የማይሰማው በውጭና በአገር ውስጥ የሚገኙ የማህበራዊና የፖለቲካ ተቃዋሚ አካሎች ናቸው ለማለት ይቻላል። ህወሓት አያሰራን አለ የሚለው እውነት ቢሆንም፤ ዘላቂ መልስ አይደለም። የሶሪያ ህዝብ በብዙ ሽህ እየሞተ መንግስቱን ከመገልብጥ አፋፍ ላይ የደረሰው በፍርሃት አይደለም። ለነጻነት ባለው ድፍረትና ህብረት ነው። የሚያበረታታው፤ የሃገራችን ህብረተሰብ ከፖለቲካ መሪወች መቅደሙ ብቻ አይደለም። የእስልምና ሃይማኖት መሪወችና አባላት ለመብታቸው ሲታገሉ፤ የክርስቲያን አባቶች በየገዳሙ ሲነሱ አብሮ የሚታገለው ወጣቱ፤ ሴቱ፤ አባቱ፤ እናቱ፤ ከተሜውና ገጠሬው፤ ወዘተ መሆኑ ጭምር ነው። የሃይማኖት ክፍሎች አገራዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸው፤ ለነጻነት አብረው መታገላቸው፤ በያቅጣጫው መተባበራቸው ፤ ለሃገርና ለነጻነት ያለው ፍላጎትና ትግል የማይገታ መሆኑን አስምሮበታል። እምቁ ሃይል መንቀሳቀስ ጀምሯል፤ ምልክቶቹ ሁሉ የካቲትን፤ ምርጫ ዘጠና ሰባትን ይመስላሉ። ሕዝቡ አስተዋይ በመሆኑ፤ የሚያስበው ከመለስ ባሻገር ነው ለማለት የሚያስደፍሩ ምልክቶች አሉ። ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥንካሬ ጎን ነው። የኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ይህን አይቀበሉም።
ከመለስ ባሻገር እንይ፤
የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ አንድ መሪ ብቻውን አገር ለመግዛት፤ ወይንም ድርጂት ለማስተዳደር አይችልም የሚለውን ተመክሮ ካለፈው ታሪኩ ተምሯል። አምባ ገነን ቢሆንም፤ መሪው ውጤት ለመቀዳጀት የሚችለው ደጋፊወችን መርጦ የስራና የጥቅም ተካፋይ በማድረግ ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ማን፤ ምን እንደሆነ በሚገባ ያውቃል። ስለሆነም፤ ከጠቅላይ ሚንስትር መለስ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ስርአቱ የፈጠረው ጠንካራ በጥቅም ላይ የተመሰረተ ድርጂትና ደጋፊወች የሉትም ብሎ አንደማሰብ ይሆናል የሚል ግምት እንደሌለው አልጠራጠርም። ህዝቡ፤ መለስ ዜናዊ ቢኖሩ ባይኖሩ፤ ስርአቱ ይቀጥላል ብሎ ያምናል። ለእኛም፤ ስርአቱ የፈጠራቸውን መተኪያወችና ተቋሞች መገንዝብ ለትንተናና አማራጭ ለመቅረጽ ይረዳናል። መተካካትን ስናይ፤ ግለሰብ ቢታመም፤ እነደማንኛውም ህያው ከዚህ አለም ቢያርፍ፤ ገዥው ፓርቲና የፈጠረው መንግስት እንዲቆዩ በቂ ዝግጂት አድርጓል። አሜሪካኖችም የህወሓት ሽግግር የረጋ እንዲሆን በማሰብ እየረዱት መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃል። ስለዚህ፤ ህወሓት “የዳበሳ ጉዞ” ሳይሆን፤ በእቅድ የሚመራ ስልት እየተከተለ ነው። የህወሓት/ኢሃዴግ ተጠቃሚወች፤ ያገኙትን ስልጣንና የኢኮኖሚ ጥቅም ከመጠበቅ ወደኋላ አይመለሱም።
ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በውስጥ የሚነጋገርበት፤ “በዳበሳ ጉዞ” የሚመራው የተቃዋሚው ክፍል ብቻ ነው የሚለውን ነው። ህዝቡ የቅንጂት መሪወች ያደረጉትን ስህተት የረሳው አይመስልም። ቶማስ ማውንቴንና ሌሎች በጀምላው እነደሚሉት፤ ስርአቱ እንደ እምቧይ ካቭ ይናዳል ማለት ዘበት ነው። ሆኖም፤ አምባ ገነን አመራርና አንድ መሪ የበላይ የሆነበት አገዛዝ መሪው ሲታመም ወይንም ሲሞት ይሸበራል፤ ይብረከረካል። እንዳየነውና እንደምንሰማው፤ አንዳንዱም አውጭኝ ይላል። ብዙወቹ፤ አስቀድመው ልጆቻቸውን ወደ ውጭ ልከዋል፤ ሃቭት አሽሽተዋል፤ ቤት ገዝተዋል። እንደሚሰማው ከሆነ፤ ፈሪወች አገር ይለቃሉ፤ ገንዝብ ያሸሻሉ። ሁሉም ይሸሻል ማለት ዘበት ነው። ዋና ተጠቃሚወችና ተቋሞች ይቆያሉ። በተለይም፤ የስለላና የመከላከያ ተቋሞች መሪ የስርአቱ ደጋፊወች/ጠባቂወች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ውጭ በስደት ከምንኖረው የበለጠ ያውቀዋል።
የኤርትርያ ተወላጆች እንዴት ተመረጡ?
የመተካካትን አስፈላጊነት፤ የጠቅላ ሚኒስትሩ ህመም አስጊ መሆኑ ሲታወቅ፤ የህወሓት የስለላና የመከላከያ የበላይ ባለስልጣኖች ያደረጉት ይገልጸዋል። አሁን ኢትዮጵያን የሚያስተዳድሩት፤ የጠቅላይ ሚንስትሩ ታማኝ የህብረምጣኔ አማካሪ፤ አቶ ነዋይ ገብረአብና የውጭ ጉዳይ ዋና የበላይ አቶ ብርሃኔ ገብረክርስቶስ–ሁለቱም የኤርትርያ ተወላጆች–የተደገፉት በመከላከያና ስለላ ድርጅቶች የበላዮች ነው ተብሎ አዲስ አበባ በሰፊው ይወራል። አሜሪካኖች እንዳሉበትም ይነገራል። ይህ የመተካካት ስልት ለህወሓት አደገኛ ሁኔታ እንደፈጠረና አነደሚፈጥር መገመት ይቻላል።በህወሓት ውስጥና በኢሃዴግ ውስጥ ፉክክር መፍጠሩ የማይቀር ነው። አገር ወዳድ በሆኑ የትግራይ ተወላጆችና በኤርትርያ ምርጦች መካከል የሚኖረው ፉክቻ መታየቱ አይቀርም። ሆኖም፤ ለጊዜው፤ የህወሓት የመተካካት መልክ በሽግግሩ የተከታታይነትን፤ የዘላቂነትን ምኞትና አስፈላጊነት ያንጸባርቃል። የአሁኑ አወቃቅር የሚያሳየው ችሎታ ሳይሆን፤ ለህወሓትታማኝ መሆን ቁልፍ መሆኑን ነው።
ታዲይ “ምን ይደረግ” የሚለው ዝንኛው የሌኒን መሰረተ ሃሳብ የሚያገለግለው እዚህ ላይ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በተከታታይ ሲጠይቀው የቆየ ጥያቄ አሁንም መልስ አላገኝም– ህዝቡ ለመብቱ ሲነሳ ተቃዋሚው ክፍልስ ምን ይሰራል? ምን ይጠብቃል?
ታላቁን ክፍተት እንሙላው፤
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መታመማቸው አከራካሪ አይደለም። የእግዚአብሄር ፍጥረት መሆናቸውን አንርሳ። ፈላጭ፤ ቆራጭ፤ በሰላሚዊ ግለሰቦች ላይ ፈራጂ፤ ሰውን አዋራጂ፤ አማራውን “አህያ ነህ” ባይ፤ ሰንደቅ አላማችን “ጨርቅ ነው” ባይ፤ “ሌብነት ጀግንነት ነው” ባይ፤ ከተፈጥሮ አደጋ ሊያድናቸው አይችልም። መልአክ ስላልሆኑ፤ ዘላለማዊ ሊሆኑ አይችሉም። ብዙ ተመልካቾች የሚመኙት በህይወት እንዳሉ የገነቡት አሰቃቂ ስርአት ተገርስሦ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነቱን ተጎናጽፎ እርሳቸውንና የቅርብ ግብረ አበሮቻቸውን ለህግ እንዲያቀርባቸው፤ እንዲፋረዳቸው ነው።
ይህ እንዳለ ሆኖ፤ በተደጋጋሚ ለማቅረብ የምፈልገው ዋና ነጥብ አለ። ይህም፤ ዛሬ እንደትላንቱ፤ አገራዊና ሁሉን አቀፍ የሆነ የተቃዋሚ ድርጂት አለመኖሩ፤ ለሽግግር የሚያበቃ፤ ትሁት፤ አገር ወዳድ፤ የማያዳላ፤ ትጉህ፤ አቻቻይ፤ ሚዛናዊ፤ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ያገባዋል ባይ፤ የኢትዮጵያና የአለም ህዝብ ብቁነቱን የሚቀበለው፤ ለመደራድር ድፍረትና ትጋት፤ ጥልቀትና አስተዋይነት ያለው አመራር አለመኖሩ ትልቅ ክፍተት ነው (Immense vacuum in national
political organization and wise and seasoned leadership)። የኢትዮጵያን ሕዝብ እንቅልፍ የነሳው ነው ለማለት ያስደፍራል።
ለዚህ ክፍተት በአስቸኳይ መልስ ለመስጠት ካልቻልን ታሪክ የሚወቅሰው ህወሓትን ብቻ ሳይሆን (በእርሱ ላይ ታሪክ ሲፈርድ ቆየቷል፤ ወደፊትም ይፈርዳል)፤ የተቃዋሚውን ዘርፍ ጭመር ነው። ራስን ከመውደድ፤ ጉረኛ ከመሆን፤ ከመከፋፈል፤ ከመጠላለፍ፤ ከሃገር በላይ ለስምና ለግል ዝና ከማጎብደድ፤ ለስልጣን ተገዥ ከመሆን የሚመጣውን ጉድ ወደጎን ትቶ ከሌላው ላይ ጉድ አለብህ ሲሉ ከመኖር የሚታየው ሁኔታ ሃላፊነት መጉደሉን ነው። የህዝብ ጥያቄ ሃላፊነት ከጎደለው፤ አይጠቅምም፤ አያስተማምንም፤ ለውጣ አያመጣም። የዚህ አይነቱ ባህርይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት አያሟላም። ባለፈው እንዳየነው፤ የህዝብን፤ በተለይም የወጣቱን ተስፋ ይበርዘዋል። እነ አንዷለም አራጌ፤ እነ እስክንድር ነጋ፤ ሌሎች፤ ባልፈጸሙት ወንጀል የውሸት ምስክር እየቀርበ፤ ለሃገራቸው መኖር አለመኖር፤ ለመላው ህዝብ ሰብአዊ መብት መከበር፤ ለነጻነት፤ ለሰው ክብር፤ ለፍትህ-ርትእ በመቆማቸው ብቻ ሲወነጀሉ እያየን፤ ይህን አስጨናቂ የአገራዊ ድርጂት አስፈላጊነት፤ የአመራር ክፍተት ለመዝጋት አሁን አለመነሳታችን በህዝብ እያስጠየቅን ነው። ለሃገርና ለመላው ህዝብ “የቆምኩ ነኝ” የሚል ብቸኛ (Opposition groups that operate in
silos) ተቃዋሚ ሁሉ እውነተኛ ገጹን ማሳየት ያለበት ልዩነቶችን ወደጎን ትቶ ለአንድ ሃገራዊ አላማ፤ ለነጻነት፤ ለእኩለንት፤ ለህዝብ የበላይነት፤ ለመድብለ ፓርቲ ስርአት፤ ተባብሮ መስራት ነገ ሳይሆን፤ አሁን በተግባር ማሳየት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ ይህ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ደጋግሞ የሚለው፤ እስካሁን የተጓዝነው “የጨለማ” ፖለቲካ ጉዞ የትም አላደረሰንም። በመለያዩታችን የሃገራችን የባህር በር ተዘግቷል። ጥገኛ ሆነናል። ህወሓት በምስጢር ተዋውሎ ከአንድ ሽህ ስድስት መቶ ስኩየር ኪሎሜትር በላይ የሚሆን ለም መሬት፤ ወንዞች፤ ተራራውች፤ የማእድን ሃብት ምንጮችን ለሰሜን ሱዳን አስረክቧል። የኢትዮጵያ ሕዝብ እየተራበ፤ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ለም መሬት ለውጭ መንግስታት፤ ድርጂቶችና ምርጥ የትግራይ ተወላጆች አዛውሯል። የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ በገፍ እንዲሰደድ አድርጓል። በገፍ ወደ መካከለኛው ምስራቅ እነደሸቀጥ የሚላኩት እህቶቻችን ለመብታቸው የቆመላቸው መንግስት የለም። የህወሓት አባላት የሰው ንግዱ ተጠቃሚወች መሆናቸውን ህዝቡ ያውቃል። ህወሓት/ኢሃዴግ፤ በአማራ፤ በኦሮሞ፤ በአዋሽ ሸለቆ፤ በሶማሌ፤ በአፋር ወዘተ ህዝብ ላይ ኢሰብአዊ በደል ፈጽሟል። በአማራው ህብረተሰብ ላይ ሲጸነስ የጀመረውን የብሄር ማጽዳትና መቀነስ አላማ አሁንም እያካሄደው ነው። በጎንደር በሁለት የአማራ ብሄረሰብ አባላት በሆኑ ወንድ ወጣቶች ላይ ህወሓት የፈጸመው የሚዘገንን ድርጊት ማንም ሊረሳው አይችልም። የሟቾችን አጽም ለመቀጣጫ ብሎ በመንገድ መጎተት ከኢሰባዊነት በላይ የሆነ አረመኔያዊ ወንጀል ነው። በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደዚህ ያለ ዘግናኝ ድርጊት የሚካሄድባት ኢትዮጵያ በ July 17, 2012, Economist, “Zenawi’s
Police State” ብሎ የሰየመው መንግስት የሚያካሂደው የመለስ ዜናዊ የጭቆና መንግስት ውጤት ነው። የአምባገነን አመራር መልክ ይህን ይመስላል።
“ነገ በእኔም ይደርሳል”፤
እኛ ብዙ ጉድና ግፍ እያየን ችግሩ ነገ በያንዳንዳችን ላይ እንደሚደርስ አልተረዳነውም። የሁለቱ ጎንደሬወች ሬሳ በአደቫቫይ በመሬት ሲጎተት፤ የተጎተተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭምር መሆኑን የተገነዘብነው ጥቂቶች ነን ለማለት ይቻላል። ክብሩ የተገፈፈው፤ የተዋረደው የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነው። የሚያሳየው ሰቆቃ፤ በምንም ለሰው ክብር ደንታ የሌለው፤ አዋራጂ የመንግስት ስርአት እንዳለ ነው። ይህ ስርአት፤ ማንኛውም ፍትህ ፈላጊ ግለሰብ ዋጋ እንደሚከፍል ደጋግሞ አሳይቷል። ታዲያ፤ እንደዚህ የመሰለውን የሰው ክብር ገፋፊ መንግስት ሊያቆየው የቻለው የራሱ ጥንካሬ ብቻ አይደለም። የተቃዋሚው ክፍል መበታተን፤ የእኛ ቸልተኝነት፤ የእኛ በረባ ባልረባው መከፋፈል፤ የእኛ መናናቅ፤ የእኛ በዘር መደራጀት፤ በብሄር የተደራጁ እንቅስቃሴወች አሁንም እንገነጠላለን፤ አብረን ለመኖር፤ አብረን አዲስ ለሁሉም የሚቨጅ ስርአት አንገነባም ማለታቸው ወዘተ እየጎዳንና የህወሓትን አገዛዝ እድሜ እያራዘመው ነው። የተከፋፈለ ቤት የጠላት መግቢያ በር እንደሚከፍት ሁሉ፤ የእኛም መከፋፈል፤ በመነጣጠል እያስመታን ነው። አደጋው ህወሓት እየለየ ሲመታን በተመልካችነት፤ “ከእኔ አልደረሰም” በሚል የሞኝ አስተሳሰብ ደጋግመን መቀበል ልማዳችን ስለሆነብን ነው። አገራዊ ድርጂትና አመራር ለዚህ ሰቆቃ መልስ ሊሰጥ በቻለ ነበር።
የኢትዮጵያና የመላው ሕዝቧ ጥልቀት ያለው ችግር (Intractable problems)፤ በውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ጠላቶችም የተደገፈ ነው። ጠላቶቻችን እርስ በእርሳችን አናክሰው ሊያጠፉን ባዘጋጁልን ወጥመድ ውስጥ የመውደቅ እድላችን የሚያሳየው የራሳችን ከመከፋፈል የመጣ ድክመትን ነው። በውስጥ፤ ሌላው ቀርቶ ህወሓት ቁመንለታል ለሚለው ለትግራይ ህብረተሰብ አልሆነም፤ ሊሆንም አይችልም። ይህ ህብረተሰብ፤ በኢትዮጵያዊነቱ የኮራ፤ ከሌሎች እህቶቹና ወንድሞቹ ጋር አብሮ ተሰለፎ የውጭ ጠላትን የመከተ፤ የባህር በሩን ያስከበረ፤ በሃይማኖቱ የጸና፤ አብሮ መኖርን ከዘረኝነት በላይ የመረጠ ነው። የኦሮሞ ህብረተስብም እንደዚሁ ነው። ለመላው የትግራይ ህዝብ ደንታ የሌለው የማፍያ ቡድን በዘረፋ፤ በመስረቅ፤ በመበዝበዝ፤ በማፈን፤ በመግደል፤ በማሳደድ፤ በመዋሸት፤ ለማዋረድ ሲል የሰውን አጽም በመንገድ በመጎተት ሃይሉን የሚያሳይ፤ ገንዝብና ሌላ ሃብት በማሸሽ የሚያምን ቡድን ነው። ስርአቱ ካልተለወጠ ሰቆቃው ይቀጥላል።
ይድነቃችሁ ብሎ፤ ለሃገራቸው የሚያስቡ፤ ችሎታና ብቃት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን እንደሌሉ አድርጎ፤ ምርጥ የኤርትራ ዘር ያለባቸውን ታዛዦች መርጦ ለወቅቱ ተተኪ ሲያደርግ ሌላውን እንደማያምን፤ እንደማያከብር የሚያሳይ አገዝዝ መሆኑን አስመስክሯል። ይህ ተራ የዘረፋ ቡድን ማንኛውንም ለመብቱ፤ ለሰላም፤ ለነጻነት፤ ለፍትህ የቆመ ሁሉ እንደጠላት ይቆጥረዋል።
እንሰብሰብ፤ እንተባበር፤
ለዚህም ጭምር ነው፤ አሁን መሰብሰብ፤ አብሮ መስራት፤ ከብሄር በላይ ማሰብ፤ በአንድ ድምጽ፤ ለአለም ህዝብ አቅዋም ማሳየት፤ አገር ቤት ካሉ አገራዊ ከሆኑ ተቃዋሚ ስብስቦች ጋር ኩታ ገጠም መሆን የሚያስፈልገው። ይህን ካላደረግን፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢታመሙም፤ ባይታመሙም፤ ሌላም አደጋ ቢደርስባቸው፤ ባይደርስባቸው ያለው አሰቃቂ ስርአት በተጠቃሚወች ይተካል። ያለው የበላይ ተጠቃሚ ባለስልጣን ቡድን “ጂብ” ይመስላል ብንል፤ መጭው/ተተኪው ደግሞ አንበሳና ነብር ሆኖ ያገኘውን ሃይልና ጥቅም በበለጠ ያስጠብቃል ለማለት የሚያስችል ሁኔታ አለ። የተከፋፈለ ተቃዋሚ እስካለ ድረስ የመለስ ዜናዊ ፍልስፍና በሌላ መልኩ ይቀጥላል።
የምእራብ አገሮች፤ በተለይ አሜሪካ፤ እንደ ሕንድና ሳውዲ አረቢያ ያሉ የመሬት ነጣቂወች፤ ስርአቱ እንዲቀጥል የተቻላቸውን ድጋፍ ይሰጣሉ። እነሱ የማያዩት፤ እኛ መግፋት ያለብን፤ የምእራብ መንግስታትን ማሳመን ያለብን፤ የህዝቡ እንቅስቃሴ በምንም የማይገታ መሆኑን ነው። ይህን ማለት በቂ ሊሆን አይችልም። እድሉን የመጠቀም ምርጫው የተቃዋሚው ክፍል መሆኑን ያለ ይሉኝታ መግፋት አገራዊ ጥሪ መሆኑን ተቀብሎ “ተባበሩ፤ አትከፋፍሉን” ማለት የሞራል ግዴታ ነው። ለዚህ፤ ታላቅ አገራዊ፤ ሁሉን አቀፍ ስብስባ በፍጥነት አካሂዶ ያሉትን ገንቢ አማራጮች ተወያይቶ በጋራ ማቅረብ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው።